ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በላይ ዘለቀ ዕዝ በጉባኤ መቋጫ ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በድርጅታዊ ማዕከላዊነት የኅልውና ትግላችንን ዓላማ እናሳካለን!!!”

ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ)
በላይ ዘለቀ ዕዝ በጉባኤ መቋጫ ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በላይ ዘለቀ ዕዝ ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም ዓመታዊ የሥራ አሥፈጻሚ ጉባኤውን አድርጓል። የጀመርነው የኅልውና ትግል ከያዝነው ነባራዊ እውነት ባሻገር፣ ብርቱ መረዳትን፣ ክህሎትንና ልዩ ልዩ የትግል ስልተ መንገዶችን መንደፍንም ጭምር አጥብቆ ይሻል። በውይይት ፖለቲካዊ አቅም ያድጋል፣ በውይይት የሃሳብ ልዩነቶች ይገራሉ/ይታረቃሉ፣ በውይይት ጓዳዊ መስተጋብሮች ይዳብራሉ፣ በውይይት አዳዲስ የአሠራር መንገዶች ይቀየሳሉ።

ከምንም በላይ ደግሞ ልዩልዩ ሥልጠናዎችን በጋራ መውሰድ አንድም መስጠት የአረዳድ ልዩነቶችን ለማጠበብ ያግዛል። በዚህ መሠረት የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በላይ ዘለቀ ዕዝ አመራሮች ለጋራ ትግል፣ ለጋራ ዓላማና ግብ በጋራ መምከርና መሰልጠን በማስፈለጉ ይህ ታሪካዊ ጓባኤ ተዘጋጅቶ በተሳካ መንገድ ተጠናቋል።

ጉባኤው ቀጠናችን ላይ የሚገኙትን አስቸጋሪ ሰንሰለታማ ተራሮችንና ቁልቁለቱን በማቆራረጥ ከሃያ ቀናት በላይ ጉዞን በጠላት መካከል አቆራርጠን የመከርንበት፣ አቅጣጫዎችን ያስቀመጥንበት፣ የጋራ መገነዛዘቦችን የፈጠርንበት ትልልቅ ውሳኔዎችን ያሳለፍንበት ታሪካዊ ጉባኤ ነው።

የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ መሪ ቃል “በድርጅታዊ ማዕከላዊነት የኅልውና ትግላችንን ዓላማ እናሳካለን” የሚል ሲሆን ድርጅታዊ ማዕከላዊነት አሁን ላይ ያለውን የተበታተነ ኃይል፣ የተበታተነ ሃሳብ፣ የተበታተነ አደረጃጀትን በአማራነት እሴት አንድም በአማራነት አስተሳሰብና በመታገያ ጉዳያችን አይለወጤ ነገረ ጉዳይ አማካይነት የሚከናወን ቁልፍ እሳቤ ነው።

የኅልውና ትግላችን እድገቱ፣ የአደረጃጀትና የኃይል ግንባታ ስፉህነቱ፣ የጠላት ደካማና ተለዋዋጭ የአጥፊነት መንገዱ፣ የቀጠናው መልክዓ ፖለቲካዊ ተለዋዋጭ እንቅስቃሴው፣ የዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ሥርዓቱ ላይ ያላቸው አተያይን በተሟላ መንገድ ማስተካከል የሚቻለው ወጥ የሆነ ማዕከላዊነቱን የጠበቀ ተቋማዊ አንድም ድርጅታዊ አሠራርን ማሳደግና ማከበር ሲቻል እንደሆነ በጽኑ እናምናለን።

ድርጅታዊ ማዕከላዊነት ተቋማዊ መርኅና አሠራር ከላይ ወደ ታች፣ በአንጻሩ በድርጅት ጥላ ሥር የሚገኙ አሓዶች፣ ግለሰቦች ከታች ወደ ላይ የሚያከናውኗቸው የሠመሩ ተግባቦቶች እንዲፈጠሩ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ድርጅታዊ አሠራሮች፣ ህግና ደንቦች፣ ነባራዊ እውነት፣ ዘመን ዘለል ልሂቅነት፣ ዓለምአቀፍ አሠራርን ያማከለ ምክንያታዊነት፣ ለህዝብ ጥቅምና ለወል ዓላማ መስዋዕት ከፋይነት ማጠንጠኛ ቁልፍ ጉዳዮቹ ናቸው። ድርጅታዊ ማዕከላዊነት እኔነትን ይጠየፋል በአንጻሩ በእኛነት፣ በአብሮነት፣ በአንድነትና በአንድ ተቋማዊ አሠራር ተገዥነት የሚጓዙት የአሠራር መሠረት ነው። ለዚህ መሰሉ አሠራር በላይ ዘለቀ ዕዝ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላትና መላው የዕዛችን የሠራዊቱ አመራሮችና አባላት የሚያምኑበትን፣ የሚያሸንፉበትን፣ ጠላትን የሚነቅሉበትን፣ የሕዝባችንን ዘለቄታዊ ኅልውና የምናረጋግጥበትን በማዕከላዊ አንድ አሠራርነት፦ አንድ አመራርነት፣ አንድ ግን የጋራ ውሳኔ ሰጭነት፣ የጋራ ጠላት ላይ ማበር መተባበርነት፣ አንድ ተቋም መፍጠርነት፣ በአማራነት አንድ መሆንነት ላይ ትኩረታችን፣ ውይይትና ሥልጠናችንን ማድረግ ችለናል።

በጥቅሉ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በላይ ዘለቀ ዕዝ በጉባኤው መቋጫ ላይ የሚከተሉትን ሦስት የአቋም መግለጫዎች በማውጣት ጉባኤውን ቋጭቷል።

የአብይ አሕመድ አረመኔያዊ አገዛዝ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመላው አገሪቱ አማራዊ ማንነት ያላቸውን አካላት ያለ አንዳች ምክንያት እንደ አውሬ እያደነ በጅምላ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ፣ ከቀያቸው ማፈናቀሉ፣ ሃብት ንብረታቸውን ማውደሙ ገሐደ የወጣ ሐቅ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ክልላችን ውስጥ ጦር አዝምቶ ያልፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት የለም።

ሕዝባችንንም በጅምላ በአየር ኃይልና በሜካናይዝድ ጦር ጨፍጭፏል፣ ዓለምአቀፋዊ የጦር ወንጀልም ፈጽሟል። እንዲሁም ለማኅበራዊ፣ ምጣኔሃብታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሕዝባችንን ዳርጎታል። በዚህ ሥርዓታዊ አውዳሚነት ሂደት ውስጥ የፋኖ መካች ትግልና እንቅስቃሴ ባይኖር ኖሮ ግፍና መከራው በመቶዎች እጥፍ ሊጨምር በቻለ ነበር። ስለሆነም በመንግሥትነት ጭምብል የሚነግደው ይህ ወንጀለኛ ሥርዓት በአጭር ጊዜ እንዲወገድ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) ማእከላዊነትን ጠብቀን የትግል መንገዳችንን ሥልታዊነት (Strategize) አድርገን ለመታገል ያለንን ጽኑ አቋም እንገልጻለን።

የኅልውና ትግላችንን የገጠመው የኃይል እጥረት ሳይሆን ያለንን ሰፊ ኃይል በአንድ አስተባብሮና አቀናጅቶ ጠላት ላይ አለመተባበር እንደሆነ የታመነ ጉዳይ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አጠገብ ካለ ወንድም ይልቅ ሩቅ ላለ አካል ከፍተን የሰጠነው ጆሯችን ብዙ ዋጋ አስከፈለን። የአንድ አማራዊ ማንነት ባለቤቶች ሆነን፣ አንድ ጠላት ኖሮን፣ አንድ ዓይነት ሞት ተደግሶልን እኛ ለምን አንድ መሆን ተሳነን ካልን ቁጭ ብለን መነጋገር አለመቻላችን ካልሆነ ሌላ ምክንያት የለንም።

“መለያየት ሞት ነው” እንዳለ ባለቅኔው መለያዬት ለተደገሰልን ሥርዓታዊ የሞት ድግስ ራስን ማዘጋጀት ነው፣ መለያየት የሕዝብን ሰቆቃ ማራዘሚያ መንገድና ጸረ ሕዝብነት ነው፣ መለያዬት ልሂቅነት ሳይሆን የዘመናችን የአላዋቂነት ጥግ ነው፣ መለያዬት በድርጅታዊ ማዕከላዊነት አለመጓዝና ትልቁን ዓላማና ግብ መዘንጋት ነው።

ስለሆነም ማሸነፊያ መንገዳችን የሕዝብን እንባ ማበሻ መሃረባችን፣ የተደበቀም የተገለጠም የጠላት አሠራርና እቅድን ማርከሻ ፍኖታችን፣ በኅልውና ትግላችን ስም በሕዝብ ላይ የሚቀልዱ ባለግል ፍላጎት አጋች፣ ሌባ ዘራፊና ተላላኪ ባንዳዎች ማጥሪያ ወንፊታችን አንድነት ብቻ ነው። ይህንን ቅዱስ ተግባር ለማከናወን ቁጭ ብሎ “እውነትን፣ እውቀትን፣ ፍጹም መተማመንን” ማእከል አድርጎ መነጋገር መቻል እንደሆነ በጽኑ እናምናለን። ለዚህ ተግባራዊ ሥራ ደግሞ የበላይ ዘለቀ እዝ እስከ መጨረሻው ድረስ ተጉዞ የማሸነፊያ ቁልፍ የሆነው አንድነት እንዲመጣ ያለንን ጽኑ አቋም እንገልጻለን።

በአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ታፍራና ተከብራ የምትኖረውን ታላቋን ሃገር ኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ተደማጭነቷን፣ ታሪካዊ ልዕልናዋን በማኮሰስ፣ በውስጥ ዓለምአቀፍ የጦር ወንጀል እየፈጸመ፣ በቀጠናው ሃገሪቷን ወደ ጦርነት አዙሪት ውስጥ ለማስገባት እየተደረጉ ያሉ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ አካሄድ የሥርዓቱን የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ድህነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ጉዳይ ነው።

የምሥራቅ አፍሪካ መልክዓ ፖለቲካ በየቀኑ መልኩንና ገጽታውን እየለዋወጠ የሚገኘውም በግንባር ቀደምትነት በብልጽግና ተናካሽ የፖለቲካ አካሄድ እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ይኸው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች ያሉት፣ የበርካታ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊና መሰል የባህል፣ የቋንቋ፣ የእምነት እንዲሁም የሥነ ልቡና ተጋሪነት ያለው በመሆኑ አብሮ የመልማት፣ ሥነ ምኅዳራዊ ተጋሪነትና ተጠቃሚነት ያለው መሆኑን እንኳን የሚያስብበት ፖለቲካዊ መርኅና ስሪት የሌለው የቀጠናው ጸረ-ሰላም ኃይል መሆኑን በዓለም አደባባይ እያሳየ የሚገኝ በመሆኑ ይህንን እኩይ እብሪተኛ ቡድን እስካልተወገደ ድረስ በውስጥም በቀጠናውም ሠላም መስፈን እንደማይችል በጽኑ እናምናለን።

ስለሆነም በውስጥ የሃገሪቱ ሁሉንአቀፍ ቀውስ እንዲስተካከል በውጭ ቀጠናዊ ቀውሱ እንዲስተካከል ቀውስ ጠማቂውን በተባበረ ክንድ ማስወገድ ቁልፉ ተግባራችን እንደሆነ ያለንን ጽኑ አቋም እንገልጻለን።

ኅልውናችን በተባበረ ክንዳችን!!!
ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በላይ ዘለቀ ዕዝ

Previous
Previous

ኢኮኖሚ ኢትዮጲያን ውድቀቱን /ፋኖ/ኤርትራ/ትግራይ

Next
Next

አፋብኃ ምኒልክ ዕዝ በዘመቻ አባ ናደው የተገኙ ድሎችን አስጠብቆ አዳዲስ ድሎችንም እያስመዘገበ ቀጥሏል! /Abebe Fentaw-AFNF’s Spoke Person