A little Girl Sexualy Abused by multiple Abiy Ahmed’s Military

ልጄን ሳገኛት እርቃኗን ነበረች። የምይዘው፣ የምጨብጠው፣ የምሆነው ጠፍቶኛል። ቀና ብላ ልታየኝ አልቻለችም። እኔን አባቷን እንኳን ማየት አፈረች። የለበስኩትን ኮት አውልቄም ሸፋፍኜ ወሰድኳት። ምን አደርጋለሁ?! ያንን ከማድረግ ውጪስ ምን አማራጭ አለኝ ?! . . . "

ይህን ያለው አንድ ምስኪን፣ የሚወዳትና የሚሳሳላት ሕፃን ልጁ የተደፈረችበት አርሷደር አባት ነው። ትናንት ምሽት ፍፁም የሚያንገበግብ፣ ፍፁም የሚያቃጥል፣ ከእንቅልፌ ያኳረፈኝን ታሪክ ሰማሁ። የዛሬ ሶስት አመት ገደማ አንዲት የ15 አመት ሕፃን መደፈሯን እና ወላጅ አባቷ "ፍትህን ፍለጋ እየተንከራተትኩ ነው አግዙኝ፣ እንደነርሱ ደህና ዘመድ የለኝም፣ ስለ እውነት የሚገደው ሁሉ ከጎኔ ይቁም፣ ከአቅምም፣ ከፍትህም፣ ከእውነትም እንደ ጎደልኩ አልቅር እባካችሁ አግዙኝ!! " የሚል ስቃይ፣ እልህና ድካም እኩል በእኩል የሚታዩበት ዜና።

በሲዳማ ክልል፣ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን፣ ዳኤላ ወረዳ፣ የ15 አመቷ ሕፃን ደጉ፤ አከባቢያቸው ላይ ያለ ለቅሶ ቤት ለማፅናናት ባመሸችበት ሌሊት "አበበ ክፍሌ" የተባለ ወደል ጎረምሳ በሶስት ጓደኞቹ እገዛ አፍኖ ወስዷት ጭካኔ በተሞላበት መልኩ አስገድዶ ደፍሯታል።

ፍርድ ቤት የደፋሪው ተባባሪ የነበሩትን ሶስት ሰዎች የ6 አመት እስር ፈርዶባቸው የነበር ቢሆንም ከ2 አመት እስር በኋላ በአመክርዎ ተለቀዋል። ዋናው ወንጀለኛ እና በህፃኗ ላይ ጥቃት ያደረሰው "አበበ ክፍሌ" የተባለው ሰው ግን እስከ ዛሬ ድረስ አልተያዘምም ለፍርድ አልቀረበምም። የልጅቱ አባትን ሕመም ያባሰውም ይህ ነበር።

ፖሊስ የህፃን ልጁን ደፋሪ ማግኘት አልቻልኩም ይላቸዋል፣ የአከባቢው ሽማግሌዎች ነገሩን በሽምግልና ካልፈታን ይሉታል። ፖሊስ ማግኘት አልቻልኩም፣ ተሰወውሮብኛል ያለውን ወንጀለኛ ሽማግሌዎቹ ከየት አመጡት?! የአባትየው ጠያቄ ነው።

"ልጄ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በደረጃ የምትወጣ፣ ብዙ ህልም የነበራት፣ ከወረቀቷ ጋር ስትላፋ የምታድር፣ አንብባ በቃኝ የማትል ጎበዝ ነበረች የሚለው ወላጅ አባቷ አርሷደር ዳንሳሞ

እውነት ከአከባቢዬ አጎደለኝ፣ ሽማግሌዎችን የማያከብር ሰው አስባለኝ፣ ያለቦታዬ አዋለኝ፣ ጽዩፍ ሰውም አደረገኝ። ከቤተሰቤ ጋር ለዘመናት የምመላለስበት ቤተክርስቲያንም ሽማግሌዎችን የማትሰማ ሰው ነህ እንዳትደርስ አለኝ፣ ከእድርም አገለሉኝ፣ ማህበራዊ ሕይወቴም ተቃወሰ፣ ቤተሰቤ ደሴት ላይ የሚኖሩ ሆኑብኝ፣ ተገለሉብኝ። የልጄን ደፋሪ በሽምግልና ነፃ ካላወጣኸው በሚል ምክንያት። በህግ መጠየቅ ያለበትን ወንጀለኛ ነፃ ሰው አድርገው ተብዬ።

በምን መልኩ ነው ይህ እውነት የሚዳኘው?! እሺ ብልስ ልጄ ምን ትለኛለች?! ከመሬቴ ውጪ ያልሸጥኩት ምን አለ?! ያለኝን ሀብት ሁሉ አሟጥጬ የተመላለስኩበት ጉዳይ ነው። በኮቴ ደሟን ጠራርጌ፣ ሸፋፍኜ ስወስዳት ቢያዩስ እንዲህ ይሉኝ ነበር?!

ሁሉም ተባበሩብኝ። የሽምግልና ወጉም ጠፋብኝ። አሁንም እሰጋለሁ። የደጌ ታናሽ 12 አመቷ ነው። ይህን አደረግክ ብለው በሷ እንዳይበቀሉኝ እፈራለሁ። መንገድ ላይ ሲያዩኝ ይሳለቁብኛል። የቁራ ጩኸት ይሉኛል። እኔ አርሷደር ነኝ። እነርሱ ሀብቱም ሹመቱም ያላቸው ናቸው።

ደጉን ማገገሚያ አቆይቼ ባመጣኋት በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደግመው ሊጠልፉብኝ ነበር። የኔ ደጉ አሁን ያለችውም ሀዋሳ እንደርሷ ጥቃት የደረሳቸው ልጆችን ሰብስቦ በሚያኖር ድርጅት ዉስጥ ነው። ከእኛ ጋር መሆን ይናፍቃት ይሆናል። አቅም የለኝም። ስለእውነት ብላችሁ ከጎኔ ቁሙ። "

የደጉ አባትን ጭንቀት የሰማችሁ ወገኖች ሁሉ እባካችሁ ድምፅ ሁኑት። #ፍትህለደጉ በሉለት። ወንጀለኛው ተገቢውን ቅጣት እስኪያኝ ድረስ ተጋግዘን እንጩህ መልዕክቴን ሼር በማድረግ እንድታግዙኝም እጠይቃችኋለሁ።

በየጊዜው የምንሰማቸው ዜናዎች አንገት ያስደፋሉ።
Via: ምናሴ ዋቆ

Previous
Previous

Hiber Radio/Report Mareshete Tsehayou

Next
Next

Hiber Radio/ the voice