የብቻዬንም ቢሆን አማራ ሆኜ እሞታለሁ!*****ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ ተበጀ እረታ አቦዬ ወልደእግዚእ እባላለሁ። ማንነቴ አማራ ነው። መገለጫዬም ግብሬም አማራ ነው።
የብቻዬንም ቢሆን አማራ ሆኜ እሞታለሁ!
*****
ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ ተበጀ እረታ አቦዬ ወልደእግዚእ እባላለሁ። ማንነቴ አማራ ነው። መገለጫዬም ግብሬም አማራ ነው።
እኔነቴን በመንደር ለማጠር ለሚፈልጉ ሰዎች ግን ስለእኔ ማወቅ ስላለባቸው መነሻዬን እነሆ ብያለሁ።
በአባቴ በአባቱ 6ኛ ትውልድ በአባ ወልደእግዚእ የሸዋ መንዝ ተወላጅ ነኝ። መንዜው እንጅልሼ ጎጃም ዳሞት ፍኖተሰላም አካባቢ መንዝ የሚባል ስፍራ የቆረቆረ ነው። ዛሬም ድረስ ቦታው መንዝ እየተባለ ይጠራል። በ6ኛ ትውልዴ የመንዝ ውሉድነቴን የተወሰኑ አማራ የሆኑ አማሮች ያውቁታል።
የአባቴ እናት እመት ሙሉነሽ ደስታ ይባላሉ። እመት ሙሉነሽ የደጃዝማች ደስታ ንጉሴ ልጅ ናቸው። ደጃዝማች ደስታ የደጃዝማች ንጉሴ ጎሹ ልጅ ናቸው። ደጃዝማች ጎሹን ከሞላ ጎደል ሁሉም ያውቃቸዋል።
እናቴ እማሆይ የሕዝብዓለም ዘለቀ ጥሩነህ በለጠ መንግስቱ ትባላለች። የልጃንበራ አማራ ናቸው። የልጅ ዘለቀ እናት እመት ፀሐይወርቅ እምሩ ቢሰወር የብላታ እምሩ ልጅ ናቸው። ከሰከላ እስከ ጅጋ ድረስ በዳግማዊ አጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስት አጥቢያ ዳኛ ሆነው ያገለገሉ ኩሩ አማራ ናቸው። የዘር ሀረግ ታሪካቸውም በአመዛኙ ከቤተ ክህነት ጋር የተያያዘ ነው። ዛሬም ድረስ አንቱ የተሰኙ ሊቃውንት ጋር የጋራ መነሻ ያላቸው ናቸው። ዝርዝሩ መታበይን ስለሚያክል ዘልየዋለሁ።
ቋሪት፣ ሰከላ፣ ቡሬ፣ ፍኖተሰላም፣ ጎንደርና አዲስ አበባ በተለያዩ የሕይወት እርከኖች ያደግሁባቸው፣ የተማርሁባቸውና የኖርሁባቸው ናቸው። የአማራ ታሪካዊ ርስት ሁሉ ርስቴ የሆነ ሁሉም የእኔ፥ እኔም ለሁሉ መሆናችን ግን ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ መቼውንም አይሆንምም!
እኔ አማራ የሆንሁት የምርም ተፈጥሯዊ አማራ ስለሆንሁ ነው። ወደ አማራ ፖለቲካ የገባሁትም ማንም አስገድዶኝ ወይንም ገፍቶኝ አልያም ጎትቶኝ አይደለም። አማራ ስለሆንሁ አማራነቴ ስለተጠቃ ይኽንን ጥቃት መመከት ግዴታዬ መሆኑን ነፍስያዬ ስለነገረኝ ብቻ ነው። የብሔርተኝነት ትግሉንም የጀመርሁት ከአብንም ከቤተአማራም ምስረታ በፊት ነው። ሊያውም እንደዛሬው አንበሳው ጀግናዬ እያለ የሚያሞግስ አልያም ጎጃሜ እያለ የሚናከስ ሳይኖር ለብቻዬ አማራ ሆኜ በወያኔ ደኅንነቶች እየታሰርሁ እየተፈታሁና እየተደበደብሁ ብዙ ዋጋ ስከፍል ኖሬያለሁ። ዋጋ የከፈልሁት ለራሴ ለማንነቴ ስለሆነ አልመፃደቅበትም። የሚገርመው አሁን እንዲህ ከሚሊዮኖች ጋር ከመሆኔ በፊት አማራ ነኝ እያልሁ በወያኔ ደኅንነቶች ፍዳዬን ስበላ የራሴው ሰዎች ደግሞ የወያኔ ሰላይ እያሉ ይከሱኝ ነበር። አብረን ብዙ ሥራዎችን ሰርተን የጋራ ሥራችንን ለንግድ ያዋሉ ሰዎች በጋራ ተመካክረንና ተስማምተን ለተልዕኮዬ መሳካት ለሽፋን ያደረግኋችውን ፕሮፓጋንዳዎች ዛሬ ለከንቱዎች ክስ ማስረጃነት ሲያቀብሉ ይውላሉ። አማራነታቸውን አሽቀንጥረው ዛሬ የሰፈር ንጉስ ለመሆን የሚፈራገጡት እነዚህ ሰዎች እኮ የሰኔ 15 ክስተትን ተጠቅመው በጥቅሉ አማራነት ላይና በግልም እኔ ላይ የፈፀሙትን ነውር ተዘርዝሮ አያልቅም። የተውነው ለአማራ አንድነት ብለን ነው። ለታሪክ መማሪያ ይሆን ዘንድ ግን አንድ ቀን እውነቱን መፃፌ አይቀርም!
የሰፈር ንጉስ ለመሆን የሚጋጋጡ ወበከንቱዎች ታዲያ ካደረሱብን መጠነሰፊ ግፍ በኋላ እንደነሱው በጭቃ እንድንዋኝ ቢፈልጉም ከአማራነታችን ማማ ወርደን በመንደር አመድ ለመንከባለል የልቡና ውቅራችን አልፈቀደምና እጅጉን ተበሳጭተው ሁሉንአቀፍ ጉንተላዎችን ቢያደርጉም ፈፅሞ አልተሳካላቸውም። መቼውንም አይሳካላቸውም። ለአማራ ከጎጃሜው በላይ ጎጃም ርስቱ ነው። ለአማራ ከጎንደሬው በላይ ጎንደር መናገሻ ምድሩ ነው። ለአማራ ከወሎዬው በላይ ወሎ መነሻ ማኅፀኑ ነው። ለአማራ ከሸዌው በላይ ሸዋ የመኳንንትነቱ ምንጭ ነው። እና ማነው በርስቴ ከዚህ መለስ አያገባህም የሚለኝ?! ማንስ ነው ከእኔ ከአማራው በላይ ስለአማራ ርስቶች ባለቤት ነኝ ባይ?!
ይህ ባለበት ሁኔታ የታላቁ አማራ ንጉስ የአጤ ቴዎድሮስ ዳግማዊ የሰማእትነት ዕለትን ለመዘከር ዛሬ የፃፍሁትን ማስታዎሻ ተከትሎ ላሜ ወለደች ሲጨፈሩ ውለዋል። በርካታ የዋኃትንም አደናግረውበታል። በወበከንቱዎች ተንኮል ተደናግራችሁ ከአማራነት ዙፋን ወርጄ በመንደር አመድ የተንከባለልሁ የመሰላችሁ ወንድሞችና እህቶች ለተፈጠረባችሁ የስሜት ስብራት ይቅርታ እጠይቃችኋለሁ። የሆነው ሁሉ አማራነትን በጽኑ አለት ላይ ከማንበር ያለፈ ግብ እንዳልነበረው ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ። የሆነው ሆኖ ግን የጋራ ታሪካችንን በውሉ በመመርመር አመዱን ቡፍ ብለን እውነቱን በማውጣት በጋራ ልንሞውና ልንደምቅበት የተገባ እንደሆነ ማስመር እፈልጋለሁ። በዚህ ሂደት ከለመድናቸው የተለዩ ኃቆች ቢኖሩ ለተጨማሪ ጥናትና ምርምር ከመትጋት ባለፈ የማዶ ለማዶ እንካስላንትያ ማድረግ ግን ፈፅሞ ያልተገባ ነው። አንዱ የሁሉም ነው፥ ሁሉም ያንዱ ነው! በዚህ ቁርጠኛ አቋም ሊኖረን ይገባል። በሁሉም ጎራ አንዱን አካባቢ የተለዬ ስም እየሰጡ ማራከስና ማንኳሰስ ግን ሥርየት የለሽ ኃጢያት ነው። ከዚህ የባሰ የስነልቦና ጦርነት ወያኔ እንኳን አማራው ለይ አላደረሰምና!
ስለአማራ የምጽፈው በደረስሁበት የእውቀትና እውነት ልክ ነው። ስለአማራ የምታገለውም በመረዳቴ ወሰን ልክ ነው። የምታገለውም እውነት በምለው በማውቀው ልክ ለአማራ ይበጀዋል ብዬ በተሰማራሁበት የትግል ዓላማ ነው። በእኔ ምክንያት አማራነት እንዲጎዳ አልፈልግም። ያመነኝ ሕዝብ፤ በፀሎት የሚያስበኝ ሕዝብ፤ የጋራ ኅልም አለን ያሉ ወንድሞችና እህቶች በእኔ ስንፍና ምክንያት አንገት እንዲደፉብኝ አልሻም። አንገት ለማስደፋትም መንደሬዎች ምን አሏቸው! የምወዳችሁና የምትወዱኝ አማራ ስለሆንሁ ብቻ ሳይሆን በእውነት ስለቆምሁ እንዲሆንም እፈልጋለሁ። በእውነት እንድወለድ እንጂ በውሸት እንድጨነግፍ በሀሰት ከጎኔ እንድትቆሙ አልሻም። የውሸት የሆነ ሁሉ አማራነትን ቢያጎድፍ እንጂ አያነግሰውም። አማራነት እውነት ማለታችንስ ለዚህም አይደል!
መንደሬዎችና ስፖንሰሮቻቸው ፍላጎታቸው ግልፅ ነው። አንድም አማራነትን በመንደር መከፋፈል፤ ሁለትም በአማራነታቸው የቆሙ ሰዎችን ገፍተው መንደሬ ማድረግ ወይንም ተማረው ከትግል እንዲርቁ ማድረግ። ለዚህ ነው ከምንዱባን የመንደር አክቲቪስቶች እስከ ፍናፍንቱ ብአዴን የማኅበራዊ ሚዲያ አመራሮች ላሜ ወለደች ሲደለቁ የዋሉት። ቤተሰብ ለመምራት እንኳን ብቁ ስላልሆናችሁ በሕግ መታገድ ላለባችሁ መንደሬዎችማ ሕዝባችንን አንተወውም!
በሞት ሸለቆ መካከል ሆነን ያልተውነውን አማራነት በመንደር አንሸጥም፤ አንለውጥም። እኔ ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ እጓለ አንበሳ ዳዊት እንኳንስ 50 ሚሊዮን አማራ አይዞህ እያለኝ የብቻዬንም ቢሆን አማራ ሆኜ ኖሬ አማራ ሆኜ እሞታለሁ። ይኼ ቃሌ ነው። ቃሉን የማያከብር ወንድ ልጅ አይፈጠር!
የፎቶ መግለጫ፦ በ1992 ዓ .ም የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ለመፈተን የተነሳሁት ፎቶ ነው። በወቅቱ የ13 ዓመት ልጅ ነበርሁ። ያኮረፍሁት ሰማያዊ፣ ነጭና ቀይ ቀለም ያለውን የአጤ ቴዊድሮስ መለያ ቀለማት የያዘ ሹራብ ለብሼ የተነሳሁት ፎቶ ተቃጥሏልና ድጋሚ ተነሳ ስለተባልሁና በወቅቱ ሹራቡን ስላልለበስሁት ተበሳጭቼ ነው። ሌላ ቀን ክፍል ውስጥ በዚያች ሹራብ ባለቀለም ፎቶ ተነስቼያለሁ። (የያኔው የባዮሎጂ መምህሬ ጋሽ ማሩ ሞላ እባክህን ፎቶዋን ላክልኝ። )
ገብርዬ፣